እንኳን ለደብረ ዘይት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

“እግዚአብሔርሰ ገሀደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም፤ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡” እግዚአብሐር ግልጥ ሆኖ ይመጣል፤ አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም፤ እሳቱ በፊቱ ይቃጠላል፡፡ መዝ.፵፱፥፪-፫
እንኳን ለዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት (ደብረ ዘይት) በሰላም አደረሳችሁ!
“ደብረ ዘይት” ማለት የወይራ ዛፍ የሞላበት፣ የበዛበት፣ የወይራ ተራራ ማለት ነው፡፡ በደብረ ዘይት ላይ የዓለም ፍጻሜ ምን እንደሚመስል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል፡፡ “እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ቀርበው ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው“? አሉት /ማቴ ፳፬፥፫/ የዓለም ኅልፈት መቼ እንደሆነና ምልክቱ ምን እንደሆነ ለተጠየቀው ጥያቄ ጌታችን ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የዓለም ኅልፈት በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የምትታወቅ እንጂ ቀኒቱ ለሰው ልጅ ተለይታ የማትታወቅ መሆኗን ተናግሯል፡፡ በዓለ ደብረ ዘይት ቤተክርስቲያናችን ከምታከብራቸው ዘጠኙ ንዑሳን በዓላት አንዱ ነው፣ እነዚኽም ስብከት፣ ብርሃን፣ ኖላዊ፣ ጌና፣ ግዝረት፣ ልደተ ስምዖን፣ ቃና ዘገሊላ፣ ደብረ ዘይትና መስቀል ናቸው፡፡
የደብረ ዘይት ዕለተ እሑድ መጋቢት ፮ ( 6 ) ቀን ፳ ፻ ፲ ፰ (2018) ዓ. ም (March 15/2026) ከደረሱት የስብሐት ነግህ፣ የኪዳን፣ የቅዳሴ፣ የስብከተ ወንጌልና የዝማሬ አግልግሎት መካከል በጥቂቱ፦