በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ አሜን!
በመላው ዓለም የምትገኙ ፤ በሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኙ ፤ በኖርዲክና ግሪክ ሀገረ ስብከት ስር የምትገኙ ፤ በሀገረ ኖርዌይ የምትገኙ ፤ እንዲሁም በደብራችን በስታቫንገር ደብረ ገነት መደኃኔ ዓለም አጥቢያ የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕደ እምነት ተከተዮች በሙሉ አባቶች እናቶች ወንድሞችና እህቶች ህፃናትም እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳቸሁ!!!
“እስመ ናሁ እዜንወክሙ ዐቢየ ዜና ፍስሓ ዘይከውን ለኵሉ ሕዝብ”(“እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ” ሉቃ.2:10)
ይህ ምሥራች የተነገረው ለሰው ልጅ ሁሉ ነው የምሥራቹን ይዞ የመጣውና ያበሠረው ደግሞ የሰማይ መልአክ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ካህኑ ዘካርያስን ፣ ቆርኔሌዎስን እና ሌሎችን ቅዱሳን የበሠራቸው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ነው
ቅዱሳኑን ያበሠራቸው ልጅ ትወልዳላችሁ ፤ ጸሎታችሁ በእግዚአብሔር ፊት ደርሷል ወይም ተሰምቶላችኋል እያለ ነው።
ይህ መልአክ ለቅድስት ድንግል ማርያም ከሁሉ የተለየ በምድር ላይ ተሰምቶ የማያውቅ አዲስ የምሥራች ፣ ትልቅ የምሥራች ደስ ይበልሽ እግዚአብሔር ወልድ ከአንቺ ይወለዳል ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ አበሠራት እርሷም “ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ” (እንዳልከኝ ይሁንልኝ) ብላ አምና ጆሮአችንና ልባችን በደስታ ሞላችው ቅድስት ኤልሳቤጥ (“ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት”ሉቃ.1:45) ብላ እንደ መሰከረችላት
ይህ መልአክ በእመቤታችን በኩል በጆሮአችን የሰማነውን አዲስ የምሥራች አሁንም በድጋሜ በትጉዎች እረኞች በኩል ለሁላችን በዓይናችን አይተን ፤ በእጃችን ዳሰን ፤ በአፍንጫችን አሽትተን ደስ እንሰኝ ዘንድ ፤ በልተነው ከእራባችን እንጸግብ ዘንድ ፤ ጠጥተነው ከጥማችን እንረካ ዘንድ ፤ ለብሰነው ከእርዛታችን እንሸፈን ዘንድ በአጠቃላይ ለሁለንተናችን መድኃኒት የሆነውን የምሥራች ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ የመሥራች አበሠረን! ይህን የምሥራች የተረዱ
1ኛ. መላእክት
የሰማይ መላእክት ልደቱን ለእረኞች አበሰሩ፤ ሰብአ ሰገልን (የጥበብ ሰዎችን) ወደ ቤተልሔም መሩ፡፡ በጌታ ልደት መላእክት ከሰው ልጅ ጋር አብረው ዘመሩ፡፡ የተወለደው ለመላእክት ሳይሆን ለሰው ልጆች ነውና መላእክት ተወልዶልናል ሳይሆን ተወልዶላችኋል አሉ፡፡
ይህ ታላቅ የምሥራች የእምነታችን መሠረት ነው፡፡ እምነታችን ከእግዚአብሔር ስለመሆኑ መገለጫው ይህ ነው፡፡
መልአኩ አስቀድሞ ለተናቁት ለእረኞች ልደቱን አበሠረ፡፡ ‹‹ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ። “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” ይሉ ነበር።›› (ሉቃ 2፡14)
አምላክ ሰው ሆነ፤ ሰውም አምላክ ሆነ፡፡ በመላእክት ዘንድ ምስጋና ተደረገ፤ በደቂቀ አዳምም ዘንድ አንድነት ሆነ፡፡ የሰው ፍቅር አገብሮት አምላክ ሰው ሆነ፡፡
2ኛ. እረኞች
እረኞች የመወለዱን ብሥራት ከመልአኩ ሰምተው ከመላእክት ጋር አመሰገኑ (ዘመሩ)፡፡ መልካም እረኛ እርሱ ነውና ልደቱም ቀድሞ ለእረኞች ደረሰ፡፡ (ዮሐ 10፡11) እረኞቹ አመስግነውም አልቀሩም፡-‹‹እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፡፡›› (ሉቃ 2፡15-18) እረኞች ልደቱን ሰሙ፤ አመሰገኑ፤ ፈጥነው ሄዱ (በሌሊት መንጋቸውን ትተው)፤ አዩ፤ ያዩትንም ለሌሎች ገለጡ፡፡ እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ። የእውነተኛው እረኛ ልደት ለትጉሀን እረኞች ተበሠረ፡፡ በግርግም ተኝቶ ከካህናቱ ከጸሀፍቱ ሳይሆን ከእረኞች ምስጋናን ተቀበለ፡፡ የበጎች እረኞች የበጉን ልደት ከሊቃውንት ከመምህራን ከነገስታቱም ቀድመው ሰምተው አመሰገኑት፡፡
3ኛ. ሰብአ ሰገል( የጥበብ ሰዎች )
የሩቅ (የምስራቅ) ነገሥታት – የጥበብ ሰዎች – ሊሰግዱለት ስጦታንም ሊያበረክቱለት መጡ፡፡ በቅርቡ የነበሩት ነገሥታት በመጣው ሠራዊት ብዛትና ‹‹የተወለደው ንጉስ›› በመባሉ ደነገጡ፡፡የጥበብ ሰዎች በኮከብ (በመልአክ) ተመርተው፤ ሁለት ዓመት ተጉዘው መጥተው፤ ሰግደውለት (የነገሥታት ንጉሥ ነውና)፤ ወርቅን ለመንግሥቱ፣ ዕጣንን ለክህነቱ፣ ከርቤንም ለሞቱ ገበሩለት፡፡ በነቢይ ‹‹የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያመጣሉ” (መዝ 71፡10) እንደተባለ የልደት (የገና) በዓል የስጦታ ቀን የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ የጥበብ ሰዎች ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው?›› አሉ፡፡ ንጉሥ ሆኖ የተወለደ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ተወልደው ይነግሣሉ እንጂ ንጉሥ ሆነው ሊወለዱ አይቻላቸውም፡፡ የጥብበ ሰዎች መወለዱንም አውቀው ስለነበር ‹‹የሚወለደው›› ሳይሆን ‹‹የተወለደው›› አሉ፡፡
4ኛ. እንስሳት
እንስሳት ትንፋሻቸውን ገበሩለት፤ በዚያ የነበሩ እንግዶች ግን ሥፍራ አልሰጡትም፡፡ ‹‹በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጥ አወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቁኝም፥ ሕዝቤም አላስተዋሉኝም››(ኢሳ 1፡3) እንደተባለ እንስሳት (አድግና ላህም) አወቁት፤ ሰዎች ግን አራቁት፡፡ በእንስሳት በግርግም መተኛቱ የትህትናው ጥግ ነው፡፡ ‹‹ወራሹ ሕፃን ሳለ ለሁሉ ጌታ ሲሆን ከአገልጋይ የሚለይ አይደለም›› (ገላ 4፡1) እንደተባለ ንጹሐ ባህርይ የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎች በሚያድሩበት በበረት ተኛ፡፡በቀዝቃዛ (ተስፋ በቆረጠ ልብ)፤ በጨለማ (ብርሃን በሌለው ኃጢአተኛ ልብ)፤ ንፁሕ ባልሆነ (ኃጢአት ባጎሰቆለው ልብ) ቦታ ተወለደ (አደረ)፡፡
5ኛ. ግኡዛን ፍጥረታት
የሁሉ ጌታ ሲወለድ እንደሰው አፍ ፣ አፍንጫ ፣ ጀሮ ፣ ዓይን እና እጅ ( 5ቱ የስሜት ህዋሳት ) የሌላቸው ፍትረታት ህብስተ ሕይወት ነው ሲሉ ህብስት ሆነዋል ፤ የበረከት ፍሬ ነው ሲሉ የበረከት ፍሬ አፍርተዋል ፤ የቃሉ ትምህርት እንደ ወተትና መዓር ነው ሲሉ ወተትና መዓር ሆነዋል።ይህንን ቅዱስ ያሬድ እንዲህ በማለት ይገልፀዋል “በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ህብስተ ሕይወት ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አሰካላ በረከት ማየ ባህርኒ ኮነት ሀሊበ ወመዓረ”( ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተራራዎች የሕይወት ህብስት ሆኑ የበረሀ ዛፎች የበረከት ፍሬ አፈሩ የባህር ውሃ ወተትና መዓር ሆነች) ይላል የክርስቶስ ልደት በረከት ነው።
በዚህ ዘመን ያለን ሁላችን
ስለዚህ ሁላችንም የተደረገልንን ድንቅ ተዓምር፣ የተሰጠንን ድንቅ ስጦታ እያሰብን ከቅዱሳኑ ጋር እናመስግን፡- “በቅዱሳን ላይ የሚያድር እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ልዩ ከሆነች ድንግል ሰው ሆኗልና፣ ኑ ይህን ድንቅ እዩ፣ ስለተገለጠልን ምሥጢር ምስጋና አቅርቡ፣ ሰው የማይሆን ሰው ሆኗልና፣ ቃል ተዋህዷልና፣ ጥንት የሌለው ሥጋ ጥንታዊ ቀዳማዊ ሆነ፣ ዘመን የማይቆጠርለት መለኮት ዘመን ተቆጠረለት፣ የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በእርግጥ ሰው ሆነ”(ቅ.ኤፍሬም የረቡዕ ውዳሴ ማርያም)
የተደረገልንን አስበን የጌታችንን ልደት
እንደ ዮሴፍና ሰሎሜ
በአንክሮ፣
እንደ ጥበብ ሰዎች በአምኃ፣
እንደ ቤተልሔም እረኞች አገልግሎታችንን በትጋት በመፈጸም፣
እንደ ቅዱሳን መላእክት በሰማያዊ ምስጋና እንድናከብር፣
ጌታ በተወለደበት በቤተ ልሔም ቤተ ክርስቲያን ተገኝተን በዓሉን በጋራ ማክበር አለብን።
የቅዱሳን አምላክ ፣ የአብ የባህርይ ልጅ ፣ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ይጎብኘን! እንደ ዛሬው የዛሬ ዓመት ያድርሰን!
መልካም በዓል
መልአከ ገነት መምህር አብርሃም ሙጭየ የእስታቫንገር ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ወኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ
አውሮፖ ኖርዌይ (ታኅሣሥ 2018 ዓ.ም january 2026)