የ፳፻፲፰ በዓለ ጥምቀት በሀገረ ኖርዌይ ክርስትያንሳንድ
“አሜሃ መጽአ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ኀበ ዮሐንስ ከመ ይጠመቅ እምኔሁ” ማቴ 3:13 (“ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ”)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስና ወደ ዮሐንስ የሄደበትን መነሻ አድርጋ በየዓመቱ ጥር ፲ እና ፲፩ ታቦታተ ኅጉን ከመንበረ ክብራቸው (ከቤተ ክርስቲያን) አንስታ ወደ ወንዝ በመሄድ የጥምቀትን በዓል በደማቅ ታከብራለች።በመሆኑም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ልጆቿም ይህንኑ መሠረት አድርገው በየአሉበት በዓሉን ያከብራሉ።
በዓለ ጥምቀት በሀገረ ኖርዌይ
የጥምቀት በዓል በኖርዌይ ሀገር በጋራ ማክበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው በኦስሎ ከተማ በጥር ወር በ 2004 ዓ.ም ነበር። በዓሉ ለኹለተኛ ጊዜ በስታቫንጋር በ 2005 ዓ.ም፣ ለሦስተኛ ጊዜ በበርገን በ 2006 ዓ.ም፣ ለአራተኛ ጊዜ እንደገና በድጋሜ በስታቫንጋር በ 2007 ዓ.ም፣ ለአምስተኛ ጊዜ በክርስቲያንሳንድ በ 2008 ዓ.ም፣ ለስድስተኛ ጊዜ በትሮንዳሔም በ 2009 ዓ.ም፤ ለሰባተኛ ጊዜ በስታቫንጋር በ 2010 ዓ.ም፤ ለስምንተኛ ጊዜ በበርገን በ 2011 ዓ.ም፤ ለዘጠነኛ ጊዜ በክርስቲያንሰንድ በ 2012 ዓ.ም፤ በ 2013 ዓ.ም እና በ 2014 ዓ.ም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በዓሉ ሳይከበር ቀርቷል።
ለአሥረኛ ጊዜ በኦስሎ በ 2015 ዓ.ም፤ ለአሥራ አንደኛ ጊዜ በስታቫንጋር በ 2016 ዓ.ም፤ ለአሥራ ሁለተኛ ጊዜ በበርገን በ 2017 ዓ.ም፤ ለአሥራ ሦስተኛ ጊዜ ዘንድሮ በክርስቲያንሳንድ በ 2018 ዓ.ም እየተከበረ ይገኛል። በእነዚህ በተለያዩ ዓመታት በጳጳሳት፣ በመነኮሳት፣ በቀሳውስት፣ በዲያቆናት እና በኖርዌይ የሚኖሩ ምዕመናንና ምዕመናት ባሉበት ተከብሯል።
የጥምቀት በዓል በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩ ዘጠኝ ዐበይት በዓላት መካከል አንዱ ነው። ይህ ሃይማኖታዊ በዓል የአንድነት የሦስትነት ምሥጢር የተገለጠበት፣ የአምላክ ትሕትና ለዓለም የታወቀበት፣ የዕዳ ደብዳቤያችን የተደመሰሰበት፣ የሰው ልጆች ልዕልና የተረጋገጠበት፣ የድኅነት በር የተከፈተበት ታላቅ በዓል ነው። ጥንታዊት ሐዋርያዊትና ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን አምላኳ ክርስቶስ የሰው ልጆች ፍቅር አገብሮት ዘጠና ዘጠኝ ነገደ መላእክትን ትቶ በዮርዳኖስ ወንዝ መካከል ቁሞ ፈጣሪ ሲሆን በፍጡሩ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን በየዓመቱ ታስባለች።
መልካም በዓል!
ስብሐት ለእግዚአብሔር ዘወለደነ ዳግመ በጥምቀቱ !!!

