እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!
እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በሰላም አደረሳችሁ!
”አነ እፈቅድ እምኀቤከ እጠመቅ ወአንተኑ ትመጽእ ኀቤየ”
(እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል እንጅ አንተ ወደእኔ ትመጣለህ? ማቴ. 3፥14)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በመላው ዓለም፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በኖርዲክና ካሪክ ሀገረ ስብከት፣ በኖርዌይ እንዲሁም በስታቫንገር ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም አብቢያ የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች በሙሉ፦ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞች፣ እህቶችና ሕፃናት እንኳን
ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል (ለብርሃነ ጥምቀቱ) በሰላም አደረሳችሁ!
መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በማኅፀን እያለ ለጌታው የሰገደና ያመሰገነ ታላቅ ነቢይ ነው። ጌታችን በአካል መጥቶ “አጥምቀኝ” ባለው ጊዜ በታላቅ ትሕትና እና ድንጋጤ ሆኖ ምስክርነቱን ሰጥቷል። በዚህ ታላቅ ዕለት የተከናወኑልን ዐበይት ተግባራት፦
• የምሥጢረ ሥላሴ መገለጥ፡ የአንድነትና የሦስትነት ምስጢር የታወቀበት።
• የአብ ምስክርነት፡ “የምወደው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት” የሚል መመሪያ የተቀበልንበት።
• የጌታ ትሕትና፡ የሰው ልጆች ሁሉ ልዕልና የታየበት።
• የውኃ መቀደስ፡ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ውኃውን ሁሉ የቀደሰበት።
• የዕዳ ደብዳቤ መደምሰስ፡ ዲያብሎስ የቀበረው የዕዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበት።
• የትንቢት መፈጸም: የነቢያት ትንቢት የተፈጸመበት
ስለዚህ ሁላችንም የተደረገልንን ቸርነት በማሰብ፤
• እንደ ቅዱስ ዮሐንስ በትሕትና
• እንደ ቅዱሳን መላእክት በምስጋና
ጌታ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ አምሳል በሆነው የታቦታቱ ማደሪያ (ጥምቀተ ባሕር) ተገኝተን በዓሉን በጋራ እንድናከብር ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
”ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን” (፪ቆሮ. ፱፥፲፭)
የቅዱሳን አምላክ፣ የአብ የባሕርይ ልጅ፣ የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በቸርነቱ ይጎብኘን! እንደ ዛሬው ለዛሬ ዓመት በሰላም ያድርሰን!
መልካም በዓል!
መልአከ ገነት መምህር አብርሃም ሙጭየ
የስታቫንገር ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ወኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ
አውሮፓ፣ ኖርዌይ
ጥር ፳፻፲፰ ዓ.ም (January 2026)
